Tuesday, 2 December 2014

ማንነት ፍለጋ! -አሰፋ ጫቦ


assefa=chaboCorpus Christi, Texas, USA
ክፍል ፩
እንዲያው ዘው ተብሎ አይገባ ነገር! ” ቤቶች!” ተብሎ” ደጆች!” ተብሎ “ይግቡ/ግባ!” ተብሎ ነው እንጅ። ጠፍቼ ስነበትኩ።ከርምኩ ሳይሻል አይቀርም።”ለመሆኑ አስፋ ጫቦ የት ገባ” ብለው በአደባባይ ከጠየቁት ወሰንሰገድ ገ/ኪዳንንና እንዳለ ጌታ ከበደን ሌሎች እዚህ በስም ያልጠቀስኳቸዉን ሁሉ አመስግናለሁ።ለክፉም ለደጉም ጠያቂ አያሳጣችህ! እኔማ ሌላ ምን እላለሁ ! የቤት ክህነት አባቶች እንደሚሉት ሱባዔ ገብቼ ነበር።ከዚያው ከቤተክህነት ተውሸ፤(ነበርኩብትምና) “ዘኀሀለፈ ሥርየት ወለዘይመጽዕ እቅበት” እላለሁ። ነጠላ ትርጉሙ “ያለፈው ይሰረዝ ይደለዝ ለመጭው መታቀብን/መቆጠብን  ስጠኝ/ስጠን!” እንደማለት ነው።በምወደው መጽሐፍ Gone with Wind   ስካርሌት ኦሐራ (Scarlet O’Hara) Tomorrow is Another Day ትላለች።። “ነገም ሌላ ቀን ነዉ” ብሎታል ተርጏሚው ነብይ መኮንን።እኔም እንድያ እንዳልኩ ይቆጠርልኝ!
ሁለት ወንድሞቼ፤ዩሱፍ ያሲን”አሳሳቢ ማንነት፤ባንድ ሀገር ልጅነት፤የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ” እሸቱ ጫቦ Gamo/Amharic/English DICTIONARY የሚል ጽፈው ታትሞ ገበያ ዉሏል።
ኩራት ኩራት አይልህም ወይ ኩራት አይለህም ወይ?
የኛ ወንድም አይደለህም ወይ  ኩራት አይለህም ወይ? የሚሊኝ
መስለኝ። አሁን የፈልግሁት የዩስፍን መጽሐፍ በሁለት ከፍየ ለማያት ነው። በመጀመሪያ፤ በዚህ ፤መጽሐፉ ኢላማ አድርጎ ሊስላት የሚመኛትን፣ የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ ለማሳየት ነው። ለዚህ ሰበብ አስባብ ከመጽሐፉ ውስጥ አገኘሁ። መጽሐፋ ዜናሁ ለጋላ በሚለው በአባ ባህርይ መጽሐፍ ይጀምራል። የአባ ባህርይ መጽሐፍ የተጻፈው ደግሞ ብርብር ነው። ብርብር ደግሞ የጋሞ አገር ነው። ጋሞ መሆኔ ደግሞ አንዳንድ የማውቀውን፤የነበር፤ያለ፤ያልታወቀ እንዳነሳ ምክንያት ፈጠረልኝ።”በልጅ አመካኝቶ ይበሏል አንኩቶ” አንዲሉ። በክፍል ሁለት መጽሐፉን ራሱን ለማስኬድ እሞክራለሁ።
ዩሱፍ ያሲን “ይህን ያማጥኩትን ልጅ ስሙን ማን ልበለው?” ቢለኝ ኖሮ ማንነት ፍለጋ!” ወይም እኔነት ፍለጋ!” በለው ባልኩኝ። አልነበርኩምና አልጠየቀኝም።
ለመሆኑ እኔ ማነኝ? የምናስበውን ያህል፤እኔ ስለእኔ ያማስበውን ያክል ቀላል ሆኖ ኣይገኝም። ከመክበዱ የተነናሳ  ወይም ይኼ “ማንም የሚያውቀው” የተወቀ የተረጋገጠ ፤ወይም ልብ ካለማለት ” አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው” “Given” ብለን እናልፍዋለን። ወይም ጥያቄው ከነአካቴው ላይነሳ ይችላል።ምነው ቢሉ ” አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው” ነዋ! ወይም ነው ብለን፤ብየ ተዘግቷል። ግና ቀን ጠብቆ፤ምክንያት ፍልጎ ከውስጥ የሆነ ቃጭል ጢ..ሪ..ሪ..ሪ ሲል ይስማል። እንሰማለን። እኔ እስማለሁ። የቃጭሉን ጥሪ ሰማሁ አልኩ እንጅ ገባኝ፤ተረዳሁት አላልኩም። መስማትና መረዳት ከዚያም ለጥቆ ገባኝ ማለት የየራሳቸዉ የሚፈጩበት፤የሚያቦኩበት፤የሚጋግሩበት፤ከዚያም በግልም ሆነ በጋራ የሚበሉበት፤ የሚሳተፉበት መስክ፤አዳራሽ፤ጞዳ፤ጎድጞዳ አላቸዉ።ለየቅሉ ናቸዉ። መስማት! ተረዳሁት!ገባኝ ቀላል አይደለም፤አይሆንም ለማለት ፈልጌ ነው።
ወንድሜ፤ዩሱፍ ያሲን መጽሐፉን የሚጀምረው ዜናሁ ለጋላ  በተሰኘው የአባ ባህርይ  መጽሐፍ ነው። የጋሞ መንኩሴ ናቸው ይላል። ናቸው እንዴ? የዚህ ጥያቄ መልስ  የዩሱፍ መጽሀፍ ላነጣጠረበት ግብም ሆነ ለኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ ለተነሱትም ሆነ ሊነሱ ለሚችሉት የሚያናቁሩ ጭብጦች ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በከፊል ቁልፉን የያዘ ነው። እኔ ነው ብየ አምናለሁ። ላስረዳ:-
አባ ባህርይ እርግጥ የጋሞ መንኩሴ ነበሩ። የብርብር ማርያም መነኩሴ ነበሩ። ጋሞ ግን አልነበሩም። የማርያምን ጽላት አቅፈው፤ሸሽገው በእምነታቸው ምክንያት ከሚያሳዻቸው ጋሞ፤ብርብር መጥተው ጥገኛ የሆኑ አማራ መነኩሴ ነበሩ።ትግሬም ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ለዚህ አሰሳ አማራ ናቸው በሚለው ብሔድ የሚሻለኝ መሰለኝ። ታሪክ ወደዚያ ስለሚያዘምም።
ብርብር የጋሞ ቃል ነው ብየ እወስዳለሁ። መሀል ጋሞ ዴሬ(አገር) ውስጥ ነውና። የአማርኛው አንድምታው  አሁን በዚህ በዩሱፍ  መጽሐፍ አንጻር ሳየው ገረመኝ። ብርብር ያው በረበረ፤አሠሠ፤ምንም አላስቀረ ፤አደባባይ አወጣው እንደማለት አይደል? “ልጅን መልአክ ያናገረዋል “ይባላል።የልጅ አንድምታም ትርጉሙ ቀና ፤ንጹሕ ማለት ነው።እየሱሱ “እንደ ህጻናት ካልሆናቸሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ዝር አትሉም” ይላል በወንጌሉ ውስጥ። ታዲያ ይህንን አፋር ፤እስላም ወንድሜን መላክት አናግረውት ይሆን የኢትዮጵያን ጛዳ ሊፈትሽ በአባ ባህርይና በብርብር ያሰጀመረው ? በል በል ያሰኘኛል።
የብርብር ማርያም ገዳም የሚገኘው፣ጋሞ፤ በደቡብ ስምጥ ሸለቆ ( Southern Rift Valley)ተራራ ምእራብ አገጩ ላይ ነው። ወደምስራቅ ፤ወደ ፀሐይ መውጫ ሲመለከቱ፤ “ወደ ምስራቅ ተመልከቱ” ይላልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዳሴ፤ የሲዳማ፤የጌዴኦ ተራሮች ከአድማስ ባሻገር ፍንትው ብለው ይታያል። ወደእምድር ሲመለክቱ ሸለቆው እብርት ላይ የተነጠፈው የአባያ ሀይቅ ይታያል። እይታው ማለዳ፤ጎህ ሲቀድ ከሆነ ደግሞ ሽህ ምላሱን አባያ ላይ የቀሰረው የፀሐይ ጨረር  ሀይቁን  የውሃ ሳይሆን የቀለማት ሽብርቅ ፤የቀስተ ደመና ሀይቅ ያደርገዋል።የተፍጥሮ  ውበት ድምቀት ማምለኪያ ቦታ ይመስላል።እኔን እንዲያ እንዳስብ ያደርገኛል። የዩሱፍ ያሲን መጽሐፍ የሚጀምረው ከዚህ  ብርብር  ማርያም ነው። ከጨንቻ ፤ከኔ ከተማ ፤የሁለት ሰአት መንገድ  ነበርና   በልጅነቴ ሄጃለሁ። ዝርዝሩ የደመቀው ሌላ ተመሳሳይ  ተራራ ላይ ቆሜ ካየሁት ነው። መልአክም ይምራው  ምናቡ አርቆ ለማየት ምቹ፤ የሰጠ፤ የተምቻቸ ከበርብር የተሻለ ቦታ ያለ አይመስለኝም። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱምነቴ እንደተጠበቀ ሆኖ!
የኦርቶዶክስ አማኞች እምነታቸውንም ነፍሳቸውን ለማዳን ከጋሞ የተሻለ ቦታ ሊኖሩም ፤ሊያገኙም የሚቻላቸው አይመስለኝም። የብርብር ማርያም ብቸኛዋ አለነበረችም። የዶርዜ ጊዮርጊስ ፤የዶይና ኪዳነ ምህረት፤የኤሌ ገብርኤል፤የቤሌ ኪዳነ ምህረት ጢቂቶች ናቸው::
ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የብርብር ገዥ መሬት ምንኛ ካድማስ ባሻገር ለማየት የስጠ መሆኑን ለማሳየት ነው። ጥንት፤ጥዋት የብርበር ማርያም፤ብሎም የአባ ባህርይ እዚህ ቦታ መምጣት ሌላ ገጽታ ፤ሌላ አንድምታም ያለው ይመስለኛል።እስቲ እንየው።
ላለፈው ከ400 ዓመታት በላይ ለሆነ ዘመናት የብርበር ማርያም፤የዶርዜ ጊዮጊስ፤የኤሌ ገብርኤል፤የዶይና ኪዳነ ምህረት፤የቤሌ ክዳነ ምህረት  በጋሞ ዴሬ (አገር) ፤አገር ሆነው፤ደብር ሆነው፤ተቀደስው ተስለሰው ኖረዋል።ኡሁንም አሉ።ያለፈ ተሪክ በቂ ምስክር ነውና ለወደፊቱም ህልዉናቸውን የእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም መቀጠሉን የሚያጠያይቅ ነገር የለም:: ሊኖርም አይችለም! ለምን ቢሉ ታሪክ ምስክር ነው!
እንደ አጋጣሚ ሆኖ፤በልጅነቴ ዲያቆን ስለነበርኩ እነዚህን አቢያተ ክርስቲያኖች ማውቅ ብቻ ሳይሆን ደጋግሜ ሄጃለሁ።ቀድሸባቸዋለሁም።ከጨንቻ በእግር ጉዞ ከ2-4 ስዐት ቢሆን ነው። የኤሌው ገብርኤል የአባቴ አገር ስለሆነ ይበልጥ የማውቀው ነው።እመድር ለምድር ተጉዞ፤ኮሮብታ ስንጥቆ የሚንደቆደቅ ጠብል ስለአለው ብልጅነቴ ጠበሉ አሸንዳ  ለሰዓታታ  ሲወርድብኝ እንደነበር አሁንም  ትዝታ ነዉ::
ጋሞ በልምድ በሚታወቀው መልኩ ሐይማኖት የለውም። ማለት የተደራጀ መጠሪያ ፤ለምስሌ እንደክስርትና፤እስልምና ፤ሂንዱ የመገናኛ ማእከል እንደ ቤት ክርስቲያን ወይም መስጊድ ለማለት ነው።
ጋሞ በአንድ አምላክ ያመልካል።ያ አንድ አምላክ የግሉም የማህበርስቡም ነው።ሳሎ ጾሳ የለዋል። የሠማዩ አመላክ ማለት ነው። ይህ ሳሎ ጾሳ ጾታ የለውም።እንደ አላህ ማለት ነዉ።በግሉ ፤በቤቱ ይህንን የሰማዩን፤ያባቱን፤የወንዙን ፤የተራራውን አምላክ ለመቀደስ ፣ለማወደስ የቤቱ ታላቅ መሥዋዕት ያቀርባል። መደበኛው መሥዋዕት ማር ነው። በዴሬዉ (አገሩ) ስም መስዋዕት የሚያቀርበው በየዐመቱ የሚመረጠው ሁዱጋ ወይም ሐላቃ ነው።
ጋሞ ዴሬ የተለያዩ ብሔረ ስቦች ያሉበት ከተሞችን ጭምር ለመጀመሪያ የሚጎበኝ የሚገጥመው የጋራ ገጠመኝ አለ።”ታሳ አሳ ዴሬ አሳ!” ይሏቸዋል። “እኔን!እኔን! የሰው አገር ሰው! ለማለት ነው። ይህ በኢትዮጵያ ባንዳንድ አካባቢዎች እንደሚታወቀው መጤ የሚል የጥርጣሬ ቃና ወይም አንድምታ የለውም። አገራችንን የማያዉቅ ሰው መጥቷልና እንዴት እናስተናገደው ነው። ሌላ ተመሳሳይወይምተቀራራቢ ባህርይ ያየሁት  ሲዳማ ህዝብ፤ብሔረሰብ ወስጥና  በሶዶ  ጉራጌዎች ዘንድ ነው። ሲዳሞ፤ለምሳሌ፤ይርጋለም፤የተለያየ ስብጥር  ብሔረሰብ የሚኖርበት ከተማ ሰላምታው “ዳኤ፤ኔሬ ቡሼ!” ብሎ እቅፍ ነው። American Hugging  TYPE የሶዶ ጉራጌም “በላሊዴ ይምጣ!” ነው የሚሉት። ”በላየ ላይ ናብኝ!” እንደማለት።
አባ ባህርይ፤ብርብር ማርያም ሌሎችም ታቦታት የመጡት እዚህ ፤እንግዳ መቀበል፤ማረጋጋት፤ማስተናገድ የተፈጥሮ ባህርዩ(pshychological makeup of the PEOPLE) የሆነ ሕዝብ መሀል ነበር። የከተማው ህዝብ፤የተለያየ ብሔረሰብ  ጥምሩ ይህንን ባህርይ የወረሰው ፤የተጎናጠፈው ከዚህ ህዝብ ነው። አማኞች እነአባ ባህርይ ወደዚያ የተሰደዱት  ዓምላክ  አሳይቷቸው፤መርቷቸውም ነው ቢሉ አይገርመኝም። የ 400 ዓመታት ተሪክ ምስክራቸው ነውና!
ከዚህ በኋላ፤ ከ400 ዓመታት በኋላ፤ወይም በዚያ ጉዞ ውስጥ የሆነ፤የተከናወነ የሚደነቅ ታሪ አለ። አሜሪካኖች አገራቸውን “Melting Pot”     “የሕዝቦች መቅለጫ ሰታቴ (ድስት)” ናት ይላሉ። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ካርተር (ሲአድ ባሬ ኢትዮጵያን ሲወር የጦር መሳሪያ ማእቀብ ያደርጉት)” We become not a melting pot but a BEAUTIFUL mosaic. Different people, different beliefs, different yearnings, different hopes, different dreams ይላሉ። ያ አንዳለ ይሁን።
የጋሞ ሕዝብ በ”ቆሞ” የከፋፈላል።ቆሞን መስርዳት አስቸጋሪ ይመስለኛል።ቆሞ በደርቁ መልክ ፤አይነት ማለት ነው።”ሔሲ አይ ቆሞ?” የተባለ እንደሆን “ይሕ ምን አይነት ነው?” ማለት ነው።በዚህኛው አባባል ቆሞ ምናልባት ቤት ማለት እንዳይሆን? “የእገሌ ቤት” እንደማለት።ወደ አስር የሚጠጉ  ቆሞዎች ያሉ የመስሉኛል። እርግጠኛ አይደለሁም።ከነዚህ ቆሞዎች አንዱ አማራ ነው።
ለማረጋገጥ ዶርዜን ጉብኙ።ከአርባ ምንጭ በ30 ደቂቃ ቦዶ የደርሳሉ።ቦዶ የዶርዜ ገበያ  ነው።የገበያ ለት የደርሱ እንደሁ እስየው ነው። ያልጠበቁትን ያገኛሉ/ያያሉ። ብቻ ቦዶ እንደርሱ “ ዶርዜ አማራ የት ነው?” ይበሉ።ማንም በጣቱ ያመለክቶታል። ትንሽ ግር ቢለው አማራ አባባሉ ቅላጼው እኛ አማራ እንደምንለው ሳይሆን አባባሉ ለየት ይላል። ለስለስ ለቀቅ ያለ ነው።ኤሌ ቢሄዱ ይህንን የጠይቁ። “ኤሌ አማራ የት ነው?” የሳይዎታል።ታሪክም መስክረው የዶርዜ ጊዮርጊስንም የኤሌ ገበርኤልንም ተሳስልመው ጠብለም ተጠምቀው ይመለሳሉ። የዐይን ምስክር ነኝና እኔን አምኖ መጓዝ ነው።
ስደተኛው አማራ በዘመናት አንዱ የጋሞ ቆሞ ሆነ።ሆኖም ለዘለዓለም ኖረ።ይኖርልም። አንዴ፤1967 ዓ.ም መስለኛል ወዳጀንና ሕግ ትምህርት ቤት የፈርንሳይኛ አስተማሪየን ሙሴ ዣክ ቢሮን  አርባ ምንጭ በአጋጣሚ አገኘሁትና ቤት ይዠው ሄድኩ።ዣክ በጋሞ ባህል መጽሐፍ ጽፏል።  “ሳሮ ሶ አሶ!” አለ። እናቴ፤መቱኬ አጆ ደነገጠች።”አሴ ታ ኤሮንታ ኑ ደሬ አሲ ዲዜ!” አለች።”ለካ እኔ ያማለውቀው አይነት የኛ አገር ሰው አለና!” እንደማለት ነው። ጋሞ ዘር፤ ሀይማማኖት ልዩነት አያዉቅም።አያውቅም ሳይሆን ሰው ሁሉ  በየቤቱ እሱ የሚያደርገውን ያደርጋል ብሎ የሚያስብ  የመስለኛል።ያንን የታወቀ ነገር አድርጎ ስለወሰደ  ከሌሎች ጋር  ላለው ግንኙነት አሉታም  አውንታም  አያመጣበትም። ክርስቲያን ያልሆነው  ጋሞ፤(ክርስቲያኑ በጣትይቆጠራልና) “ጋብሬሌ አሾ!ጎርጊሴይ  በይን !” እያለ  ሲምል  መስማት  የተለመደ ነዉ።”የገብርኤልን ስጋ! ግዮርጊስ ባወቀ!” ማለቱ ነው። እንዳልኩት በክርስትና አማኝ ሆኖ ሳይሆን በዚያ አመኙን ማስተናገዱ ነው። ለመቻል፤ ለመቻቻል ከዚህ የላቀ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። ከተገኘማ እሰየዉ!ነዉ።
የዩሱፍ ያሲን መጽሐፍ የታሪክ መጽሐፍ አይደለም።የማሕበራዊ ሳይንስ መጽሐፍም አይደለም። የስነ ልቦና መጽሐፍም አይደለም።ከሁሉም በላይ የፖለቲካ መጽሐፍ አይደለም።ወይም እነዚህን ሁሉና ሌላም ሌላምአለው።የኢትዮጵያን ታሪክ፤ተረት፤ተርት መስል ታሪክ፤የባህል ፤የሐይማኖት፤የጎሳ ፤የብሔር፤ ብሔረሰብ፤የመንግስት ግኑኙነት፤ግጭት፤መፋጀት፤መስማማት፤መፋለስ የዘክራል።ሊዘክር ይሞክራል።ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ውስብሰብ ስምና ወርቅ ፤ማለፊያው፤መጥፎው፤አስጸያፊው አብሮ የቦካበት፤የተጋገርበት፤የተበላበት ፤የተባላበት አገር ስለሆነች  አጥነት ጉልጥምትዋ ውስጥ ገብቶ ለማሳየት መሞከር ቀላል የቤት ሥራ አይደለም።ሆኖም የዩሱፍን አቀራረብ ወድጀዋለሁ። በባለቤትነት፤በኩራት፤በፍቅር፤በልበ ሙሉነት ነው የሚዳስሰው።ይህ ደግሞ ማለትም አንድ አፋር ከዳር አገርነት ይልቅ የመሐል አገርን ሸማ ተላብሶ መናገሩ፤መጻፉ የበለጠ እንድናዳምጠው የሚገፋፋን ይመስለኛል።ከታሪክ አንፃር ስናየው ከዚህ ወግኖ ይሕንን ለራሱ ፤ለብሔረስቡ ሊያስገኝ ነው የሚል ጣት እንዳንዘርጋ የሚያቅበን ይመስለኛል። ለዚያውም ለማሰርጃ ሊቃውንቱን ከየአህጉራቱ “ዘከመ ይቤ” ብሎ ጠቅሶ ነው።የአገራችንንም ጸሐፍት ወፈሪሳውያን ሊሳይ ይሞክራል።እንደኔ እንደኔ የዩሱፍያሲን”አሳሳቢማንነት፤ባንድ ሀገር ልጅነት፤የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ” ማንበብ ነው። ውስጣችንን የሚቦርቡር፤ከዚህም ውስጥ ከሚያለያየን ይልቅ የሚያስተቃቅፈን ያመዝናል የሚለውን ለማሳየት ስለሆነ:: ያንን መየት መቻል ደግሞ ሙሉ ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ የመስለኛል።
በተረፈ ጋሞን፤አባ ባህርይን፤ብርብር ማርያምንና ሌሎች ስደተኛ አብያት ክርስቲናትን ያነሰሁት “ይኸም አለ!” ለማለት ነው።”ይኸም አለ ለካ!” እንድትሉም ነው። “ለካ መቻቻል ይቻላል!” እንዲባልም ነው። የወገንኝተኝነት ጠረን ካለው/ ካያችሁ “አይ የሰው ነገር!” ብሎ ማለፍ ነው።
በተረፈ  የነዚህ አብያተ ክርስትያናት  ንዋየ ቅድሳት የሚቀመጠው እዚያው ጋሞዎቹ ቤት ነው። ቄሴ ገበዝ፤አቃቤ ንዋይ መሆናቸው ነው። የዶርዜው ጊዮርጊስ  የሚቀመጠው ሐላቃ ጩባሮ ቤት ነው ሲባል ልጅ ሆኜ የሰማሁ ይመስለኛል። የዳይና ኪዳነ ምኅረት ንዋየ ቅድስታ የሚቀመጥበት ቤት ካንዴም ሁለቴ የበላልሁበት የጠጣሁበት ነው።
የጋሞን በር ከፍቶ መቀበል ያጎናጽፋችሁ! ምርቃት ሊሆን ይችላል?
በክፍል ሁለት ያገናኘን
ይነጋል
እናት ፍቅር ሐገር
ጥቁር ሸማ የለበሰ
ለምለም ምድር ተዘርግቷል፣
……………………………!
ሕዝብ አንቀላፍቷል፣
ሕዝብ ውስጥ
ታሪክ ተኝቷል፣
ታሪክ ውስጥ
እውነት አዛግቷል፣
እውነት ውስጥ
አርነት አለ . . .
ይነጋል እንዲህ እያለ!!
ይነጋል!

መሬታማ ባዶ ነው፤ላለማው የሚለማ፤
ለተስማማው የሚስማማ፤
ዥረቱም ግድ የለውም፤ቦይ ለማሰለት ይፈሳል፤
ተራራውም ደንቆሮ ነው ፤ለቦረቦረው ይበሳል፤
መሬቱም አይደለም ይኔ ልጅ፤እድርተኛው ነው አገርሽ፤
ስትቸገሪ ታድጎ፤ስትታመሚ አስታሞ፤ስትሞች አፈር የሚያልብስሽ፤
ብእጅሽ ያለ ብሩህ ጽጌ፤ሰው ነው ልጄ ሀገርሽ፤
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ።
ከዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ሀገር ማለት የኔ ልጅ የተወሰደመሬታማ ባዶ ነው፤ላለማው የሚለማ፤
ለተስማማው የሚስማማ፤
ዥረቱም ግድ የለውም፤ቦይ ለማሰለት ይፈሳል፤
ተራራውም ደንቆሮ ነው ፤ለቦረቦረው ይበሳል፤
መሬቱም አይደለም ይኔ ልጅ፤እድርተኛው ነው አገርሽ፤
ስትቸገሪ ታድጎ፤ስትታመሚ አስታሞ፤ስትሞች አፈር የሚያልብስሽ፤
ብእጅሽ ያለ ብሩህ ጽጌ፤ሰው ነው ልጄ ሀገርሽ፤
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ።
ከዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ሀገር ማለት የኔ ልጅ የተወሰደ
ሕዝብ አንቀላፍቷል፣
ሕዝብ ውስጥ
ታሪክ ተኝቷል፣
ታሪክ ውስጥ
እውነት አዛግቷል፣
እውነት ውስጥ
አርነት አለ . . .
ይነጋል እንዲህ እያለ!!
ይነጋል!
posted By Daneil Zeleke

No comments:

Post a Comment