እኔም ሃና ነኝ ( ሄኖክ የሺጥላ )

እንድ ነገር ለማከል ብዙ ሰዎች ” እኔም ሀና ነኝ ” ማለት ጀምረዋል ፣ ያዝልቅላችሁ ፣ ታዲያ በነካ እኔነታችሁ ” እኔም ራሴ እኔ ነኝ !” በሉኝ ። ክርስቶስ ተመልሶ ቢመጣ ” ሰው ራሱን ሳይሆን ሌላ ሰው መሆን እንደምን ይቻለው ይሆን ?” ብሎ ያስተምር ነበር ። ለነገሩ ድጋሚ ክርስቶስ መጥቶ ለኛ ቢሰቀል፣ ለምን ተሰቀለ ብለን ከስቅለቱ እና ከደሙ ተምሳሌተ ትምህርት በመውሰድ ፈንታ ” እኔም ክርስቶስ ነኝ !” የምንል ይመስለኛል ። ከቻልን ያልሆነውን አንሁን ፣ ወይ ደሞ ነን ስንል ሆነን ብቻ ከሆነ ይሁን ።
አንድ ጥያቄ አለኝ ። የሃና ጉዳይ ያገባኛል ያሉ ድህረ ገጾች ” የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ማለት እንዴት ተሳናቸው ?” በሃና ስቃይ የተቆጡ እና ያነቡ አይኖች እንዴት ስለ ህጻን ነብዩ ለመናገር ፈሩ ? ሀና ፍትህ ያስፈልጋታል ያሉ አንደበቶች እንዴት የሽብሬ ወይም የ በቀለ ገርባ ወይም የእስክንድር መታሰር ብሎም የእስሩ ኢ ፍትሃዊነት አልታይ አላቸው ? ከሀናነት በፊት እንዴት ራሳቸው ፍትህ እንደሚያስፈልጋቸው መጠየቅ አቃታቸው ። ሃናን ነኝ ስንልስ ምን ማለታችን ነው ? ሃና ላይ የደረሰው እኔ ላይ እንደደረሰ ያህል ነው ማለት መሰለኝ ? ይደለም ? ከሆነ ዘንዳ ታዲያ “ታላቁ” ( በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ይሁን ታላቁ የሚለው ቃል ) አዎ ታላቁ የገነት ሰይጣን ክርስቶስን ” እስኪ ይሄን ድንጋይ ዳቦ አድርገው?” ሲለው ክስቶስ ” ሰው በእሕል ብቻ እንደማይኖር ! ” ያስረዳዋል ! እኔ ከክርቶስ የተማርኩት ይህንን ነው፣ ነጻነት እኔም አከሌን ነኝ በማለት አይገኝም ፣ በመሆን ብቻ !!! አንዳንድ ሰዎች ከክርስቶስ ተማርን ብለው የሚሉት ስለ ገነት ማሰብን ነው ። ሰው ሆይ አጠገብህ ያለውን ገሀነም የሙጥኝ ብለህ እንዴት ስለ ገነት ታወራልህ ? ሰው ሆይ ለኢትዮጵያም እንደ ሃና እንጮኸላት ዘንድ ኢትዮጵያስ ሀገርህ ታክሲ ውስጥ ትደፈር ወይ ? አደጋ የማያደርስብንን ነገር ብቻ እየመረጥን የነጻነት እና የመብት ተሙዋጋች መምሰል ማስመሰሉን እናቁም ። አዎ የሃና ቁስል ፣ በተደፈረችበት ሰዓት ያሰማችው ጩኸት ፣ የፈሰሰው ደሟ ሁሉም ያማል ፣ ያስቆጫል ፣ ያበሳጫል ። ግን ታዲያ እኮ ፍትህ ላንድ ሰው ከተጉዋደለ ለሁሉም እንደተጉዋደለ ነው ። እኔ ሃናን ነኝ ስትል ” በእውነት ግን ነኝ ወይ ብለህ ራስህን ለመጠየቅ አንድ ሰከንድ ይኑርህ ” እኔ ክርስቲያን ነኝ ስትልም እንዲሁ ፣ እኔ ሙስሊም ነኝ ስትልም እንዲሁ ። እያሳሰበን ያለው የፍትህ መጉዋደል ሳይሆን የተጉዋደለው ፍትህ ለመጮህ ይመቻል ወይስ አይመችም የሚለው ስለመሰለኝ ነው ። አጠገብህ ያለውን ወንድምህን ሳትወድ እኔን ያላየከውን እንዴት ልትወድስ ትችላለህ ያለው አሁንም ክርስቶስ ነው ! በ ፌስ ቡክ ገጾቻችን ላይ የለጠፍናት ሃና አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለበትን የ ሞራል ውድቀት እና የስርዓቱን ዋልጌነት ያሳያል ብላችሁ መቼም ተሯሩጣችሁ እንደማታነሱት ነው፣ የሃና ደም የስርዓቱ ጭፍግግ የሞራል ድቀት ያፈሰሰው ድንግልና ነው፣ ሃና የተደፈረችው ሳትወለድ ነው ፣ ሃና የተደፈርችው የዛሬ 23 ዓመት ነው ፣ ሃና ክብሩዋ የተዋረደው ፣ ጭኑዋ በጉልበት የተፈለቀቀው ዛሬ አይደለም ፣ ትናንት ነው ፣ አጉራ ዘለል ፣ ጥራዝ ነጠቅ ፣ እና ቦዘኔ ስርዓት እና መሪ ኢትዮጵያን መምራት የጀመሩ ቀን ነው ፣ የሃና ቀሚስ የላላው ። የሃና እናት መቀነት የተፈታው ፣ በ ሬዲዮና በቴሌቪዥን ሕዝቡን የሚሳደብ መሪ የተፈጠረ ለት ነው ፣ ሃና ከተደፈረች ቆይታለች ። ሃናን የሚደፍር ስብእና ያለው ትውልድ ሲፈጠር ፣ እንደዛ አይነት ትውልድ ኮትኩቶ ያሳደገ ስርዓት ሲፈጠር ሃና ተደፍራለች ። ዛሬ ብዙ ሀናዎች ታስረዋል ፣ ብዙ ሃናዎች ተገድለዋል ፣ ብዙ ሃናዎች ገና ይታሰራሉ። ወይንሸት ማን መሰለች ሃና እኮ ነች ፣ ርዮት ማን መሰለች ሃና ራሷ ነች ። እና ሃና ነን ስንል የሚያሳስር እና የማያሳስር እየመረጥን ሳይሆን የሆነውን እና የሆ—ነውን መሆን አለበት ። ነጻነታችንን ካላስመለስን ሀገር ሃና ትሆናለች መርዎቹዋ ደፍሪዎቹዋ !!!!
አትርሱት ሕዝብ በቁጥርም በመንፈስም ከመንግስት ይበልጣል ስለዚህ ሕዝብ ከቆረጠ ያሸንፋል ። ጊዜ የመከራ መለኪያ ቁና ቢሆን እንጂ ያለመቻላችን መገለጫ አይሆንም ! እንበርታ !!!! ከ ጨቁዋኞቹ ሳይሆን ከተጨቁዋኞቹ ጎን መቆም ነው ሃናነት ፣ ሀናነት ትግል ነው ፣ እምቢ ማለት ነው ፣ ውስጡ ሞት ቢኖርበትም ! እኔ ሃናን ነኝ ስንል ፣ በሞት ጥላ ስር እንኩዋ ብሄድ ሞትን አልፈራም ብሎ ማለት ነው ። አንድ ወዳጄ እንዳለው ” ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተደፍሯል! ዴሞክራስ፣ መልካም አሥተዳደር፣ ፍትህ፣ ነፃ ምርጭ እና የህግ የበላይነት ያልተከበረበት አገር አገርቷም ህዝቧም በግዳጅ የተደፍሩ ናቸው።”
posted By Daneile Zeleke
No comments:
Post a Comment